Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አሜሪካ የሁቲ ታጣቂዎችን በድጋሚ በዓለም አቀፍ አሸባሪነት ፈረጀች

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የሁቲ ታጣቂዎችን በዓለምአቀፍ የአሸባሪ ድርጅት ዝርዝር ውስጥ በድጋሚ ማስገባቷ ተሰምቷል፡፡

የጆ ባይደን አሥተዳደር ታጣቂዎቹን በዓለም አቀፍ አሸባሪነት ለመፈረጅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን በድጋሚ ያጤነው÷ የሁቲ ታጣቂዎች ጠንካራ ድጋፍ ስላላቸውና በቀይ ባሕር ቀጣና ተደጋጋሚ ጥቃቶች በማድረስ ዓለም አቀፍ ሥጋት መሆናቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝም÷ ታጣቂዎቹ ባለፉት ወራት በአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች፣ በቀይ ባሕር እና ዔደን ባሕረ-ሠላጤ በሰፈሩት ዓለምአቀፍ የባሕር ኃይል መርከቦች ላይ በርካታ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታውሷል፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ጄክ ሱሊቫን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ ሁቲ የዓለምአቀፉን የባሕር ንግድ መሥመር አውኳል ፤ በባሕር የመንቀሳቀስ ነፃነትንም ገድቧል፡፡

ፍረጃው ሁቲ በንግድ ገበያው ውስጥ የሚያደርገውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ለመገደብ እና በመነጠል ለመምታት ያለመ ነውም ብለዋል፡፡

አሜሪካ በሁቲ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በቀይ ባሕር እና ቀጣናው በምትጥለው ማዕቀብ የየመን ንጹሐን ዜጎች÷ በምግብ፣ መድሐኒት እና ነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንዳይጎዱ ፍረጃው ከግምት ውስጥ ማስገባቱንም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ለሰብዓዊነት ሲባል ከዛሬ ጀምሮ የሚጸና የ30 ቀናት የእፎይታ ጊዜ መሠጠቱንም ነው በመግለጫቸው ያመላከቱት፡፡

የትራምፕ አስተዳደርም የሁቲ ታጣቂዎችን በዓለምአቀፍ የአሸባሪ ቡድን ዝርዝር ውስጥ አካቶ እንደነበር አስታውሶ አል-አረቢያ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version