ዓለምአቀፋዊ ዜና

ዓለም በ2050 በዓየር ንብረት ለውጥ 12 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ታጣለች ተባለ

By Meseret Awoke

January 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም በ2050 በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 12 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር እንደምታጣ ተገለጸ፡፡

ሪፖርቱ የወጣው በዓለም የምጣኔ ሐብት ጉባዔ ላይ መሆኑንም ስፑትኒክ አስነብቧል፡፡

በተጠቀሰው ዓመት የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍም ተመልክቷል፡፡

በሞቃታማ የዓየር ንብረት ቀጣና ባሉ ሀገራት የሚኖሩ 500 ሚሊየን ያህል ሰዎችም በዚሁ በሚዛመቱ እንደ ወባ ፣ ዴንግ እና ዚካ ያሉ በሽታዎች እንደሚጠቁ ነው የተጠቆመው፡፡

ሪፖርቱ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር ይመዘገባል ብሎ የተነበየው ከጎርፍ እና ከድርቅ የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተያይዞ መሆኑም ተነግሯል፡፡

በጎርፍ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ሲጠቆም በድርቅ ደግሞ የ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ሕይወት ይቀጠፋል ተብሏል፡፡

ዓለም 12 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላሩን የምታጣው ከሙቀት መጨመር ፣ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋ ጋር በተገናኘ በምታስተናግደው የምጣኔ ሐብት ተፅዕኖ መሆኑንም ያሳያል የሪፖርቱ አሃዛዊ መረጃ፡፡

በዝርዝር ለመግለፅ ያህል ÷ ሙቀት 7 ነጥብ 1 ትሪሊየን ፣ ድርቅ 3 ነጥብ 2 ትሪሊየን እንዲሁም ጎርፍ 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ዶላሮች ዓለማችንን ያሳጧታል፡፡

ተፅዕኖው በቀዳሚነት የእሲያ ሀገራትን ሲጎዳ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆኑም ነው ሪፖርቱ ያመላከተው፡፡

በዓየር ንብረት ለውጥ የእሲያ ሀገራት ÷ 3 ነጥብ 5 ትሪሊየን፣ አውሮፓ ÷ 2 ነጥብ 6 ትሪሊየን እንዲሁም ደቡብ አሜሪካ ÷ 2 ነጥብ 2 ትሪሊየን ዶላሮች ያጣሉ ተብሏል፡፡