አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በፈረንጆቹ 2023 መጨረሻ ወደ ከ4 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ የፈጠራ ባለቤትነትን በመያዝ የመጀመሪያዋ ሀገር መሆን መቻሏ ተገልጿል፡፡
ይህም ከዓመት ዓመት በ22 ነጥብ 4 በመቶ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር እንዳደረጋት የሀገሪቱ ብሔራዊ አዕምሯዊ ንብረት አስተዳደር አስታውቋል።
የአስተዳደሩ ምክትል ኃላፊ ሁ ዌንሁይ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የፈጠራ ባለቤትነት ምዝገባዎች ከጠቅላላው ከ40 በመቶ በላይ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
በዚህም ቻይና ትክክለኛ የፈጠራ ባለቤትነትን መያዟን እና ለዓለም አቀፍ ፈጠራም ቀጣይነት ያለው አስተዋፅኦ እንዳበረከተች ያሳያል ብለዋል፡፡
የሀገር አቀፍ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞች፣ አነስተኛና መካከለኛ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች 2 ነጥብ 13 ሚሊየን የፈጠራ ባለቤትነት መብት መያዛቸውንና ይህም በዓመት 24 ነጥብ 2 በመቶ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡
የፈጠራ ባለቤትነት መብት እድገቱም በራስ ፈጠራ ከፍተኛ ጥራት ያለው ልማት እንዲጎለብት ማድረጉን አያይዘው መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
በተጨማሪም በፈረንጆቹ 2023 መገባደጃ ላይ በቻይና ውስጥ አጠቃላይ ተቀባይነት ያለው የፈጠራ ባለቤትነት መብት ከ4 ነጥብ 99 ሚሊየን በላይ የነበረ ሲሆን በሀገሪቱ ያሉ ትክክለኛ የንግድ ምልክቶች ቁጥርም 46 ነጥብ 15 ሚሊየን መድረሱን ሁ አብራርተዋል።