ቴክ

ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መር ልማትን ማረጋገጥ የሀገር ህልውና ጉዳይ ነው – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

By Shambel Mihret

January 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መር ልማትን ማረጋገጥ ምርጫ ሳይሆን የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

የሚኒስቴሩን ተግባር እንዲሁም ይዘቶች፣ ፖሊሲዎችን፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጅ ትኩረቶችና የተቋሙ ስምሪቶችን በሚመለከት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች፣ ለአምባሳደሮች፣ ለቆንስላ ጄኔራሎች በተዘጋጀ የውይይት መደረክ ላይ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲን በመተግበር ረገድ ከዲፕሎማቶች ምን ምን ጉዳዮች እንደሚጠበቁ አመላክተዋል።

የፖሊሲው ተልዕኮ ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምቹ ሥነ-ምህዳር በመፍጠር ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ለሥራ ዕድል እና ሀብት ፈጠራ እንዲሁም ለሀገራዊ ምርት ዕድገት ያለውን ድርሻ ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡

የተቋማት ትስስርና ትብብርን በማጠናከር ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አጋርነትን እና ተጠቃሚነትን ማሳደግ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ልማት ላይ ተሳትፏቸው እያደገ እንዲሄድ ማድረግ ተቋሙ የሚያከናውነው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በዘርፉ ቀጣናዊ ትብብርን እና ትስስርን የሚያበረታቱ አደረጃጀቶችና የአሠራር ሥርዓቶች መዘርጋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው መሰራት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

በቀጣይ ሁሉም የድርሻውን በመውሰድ ተቋማቸውን ማገዝ እንዳለበት መግለጻቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡