Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በትራፊክ አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ሸበሌ ወረዳ በተከሰተ የትራፊክ አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በፋፈን ዞን ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ደኅንነት ኃላፊ የሆኑት ሻፊ ዓረብ መሐመድ እንደገለጹት÷ ከሟቾች በተጨማሪ በ12 ሰዎች ላይም የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችም በጅግጅጋ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አደጋው የተከሰተው ከጅግጅጋ ከተማ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ “ሚኒባስ” ተብሎ በተለምዶ የሚጠራው መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ከሸበሌ ወረዳ አቅጣጫ ሲመጣ ከነበረ በተለምዶ “ሲኖ ትራክ” እየተባለ የሚጠራው የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨታቸው  ነው ብለዋል፡፡

የአደጋው መንስዔ እና በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠንም እየተጣራ መሆኑን ለሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version