አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከለውጡ በኋላ የተሰሩ ፕሮጀክቶች ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንደዚሁም የሀገር ገፅታ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅዖ ያላቸው የቱሪስት መዳረሻ እየሆኑ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ከንቲባዋ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነትና ክትትል በሀገር ወዳድ ልበ-ቀና ባለሃብቶች ድጋፍ የተጀመረው የገበታ ለሀገር ንቅናቄ አካል የሆነው የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር በመመረቁ የተሰማቸው ደስታ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልፀዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ “ያሉንን ሃብቶች በማየት አዕምሮ እና እጅን አቀናጅቶ በማልማት ከገበታ ለሸገር ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ከለውጡ በኋላ የተሰሩ ፕሮጀክቶች ለሃገራችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንደዚሁም የሀገር ገፅታ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅዖ ያላቸው የቱሪስት መዳረሻ እየሆኑ ነው” ብለዋል።
ይህ የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እውን እንዲሆን ላስቻሉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)፣ በፕሮጀክቱ ላይ ለተሳተፉ፣ አስተዋፅዖ ላደረጉ ባለሃብቶች እና ላስተባበሩ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡