የሀገር ውስጥ ዜና

ፋና ላምሮት 4ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ነገም በ2ኛ ሳምንት ውድድሩ ይቀጥላል

By Feven Bishaw

January 12, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው ቅዳሜ በደማቅ ስነ-ስርዓት የጀመረው ፋና ላምሮት 4ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ነገም በ2ኛ ሳምንት ውድድሩ ይቀጥላል።

በተወዳዳሪዎች እለታዊ አቀራረብ ላይ ትኩረት ያደረገው ፋና ላምሮት በ4ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር የምዕራፍ 13፣ የምዕራፍ 14 እና የምዕራፍ 15 አሸናፊዎችን በአንድ ያገናኘ ነው።

በነገው የ2ኛ ሳምንት የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር የምድብ ሁለት 8 ተወዳዳሪዎች ከኮከብ ባንድ ጋር በሁለት ዙሮች ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ።

በዚህኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ፋና ቴሌቪዥን ለመጀመሪያ ጊዜ አንደኛ ደረጃን ለሚያገኝ አሸናፊ የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ደግሞ የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሽልማት ነው የተዘጋጀው፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ፋና ላምሮት ሙያዊ ስነ-ምግባር ያላቸው ድምፃውያን መፍለቂያ እንዲሆን እና ከገንዘብ ሽልማቱም በላይ ተወዳዳሪዎች ከዳኞች እና ከውድድሩ በሚያገኙት ልምድ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ እየሰራ ነው፡፡

የፋና ላምሮት 4ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ የነገ የ2ኛ ሳምንት ውድድርን በቀጥታ ስርጭት ተመልካቾች ከ6:00 ሰዓት ጀምሮ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች፣ በፋና ቴሌቪዥን እና በኤፍም ኤም 98 ነጥብ 1 በቀጥታ ሥርጭት እንዲከታተሉ ተጋብዘዋል፡፡

ተመልካቾችም በዕለቱ የሚገለፀውን የተወዳዳሪዎች ኮድ በመጠቀም በ8222 የsms መልዕክት በመላክ እንደተለመደው በንቃት ይሳተፋሉ።

በለምለም ዮሐንስ