Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለቀጣዩ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 76 ሺህ 192 ችግኝ ጣቢያዎች ወደ ስራ ገብተዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለቀጣዩ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 132 ሺህ 226 የችግኝ ጣቢያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ አሁን ላይ 76 ሺህ 192 ችግኝ ጣቢያዎች ሥራ መጀመራቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዓብይ ኮሚቴ የ2015/16 ዓ.ም አፈፃፀም እና የ2016/17 ዕቅድ ላይ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍን በሚመለከት ውይይት አካሄዷል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በመከላከል የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግና ዘላቂነት ያለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ትልቅ ሚና እንዳለው ተገልጿል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አረንጓዴና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት መሠረት የጣሉ ስራዎች እንደተከናወኑ ተጠቅሷል፡፡

በምዕራፉ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና ተግዳሮቶችን በማረም በ2015 ዓ.ም ሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረግ ተችሏልም ተብሏል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት÷የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ችግኝ ከመትከል ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ብለዋል፡፡

በኮፕ 28 ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ያሳየችው ውጤት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለሀገር ገፅታ ግንባታ ትልቅ ሚና የተጫወተ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር132 ሺህ 226 አዳዲስ እና ነባር የችግኝ ጣቢያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት መታቀዱ ተገልጿል፡፡

ከእቅዱ ውስጥም እስካሁን 76 ሺህ 192 የችግኝ ጣቢያዎች ወደ ስራ መግባታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version