Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከወቅቱ ጋር እንዲራመድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል – ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከወቅቱ ጋር እንዲራመድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዘዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት ዓውደ ርዕይ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ የ116 ዓመታት የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት ሀገር ናት ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፥ በእነዚህ ዓመታትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ክብር በዓለም ዙሪያ ሲያስጠብቅ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ዓውደ ርዕዩ የዲፕሎማሲያችንን እውነተኛ መልክ የሚያሳይ ብቻ ሣይሆን የመጪውን ዘመን የዲፕሎማሲ ጉዞ የምንዳስስበት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የውጭ ፖሊሲ የአንድ ሀገር የውስጥ ሁኔታ ነጸብራቅ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ፥ የዛሬው ኤግዚቢሽንም ይህን ያረጋግጣል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ሥነ መንግስት አሰራር ልምድ ያላትና ሉዓላዊነቷን ሳታስደፍር፣ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር መሆኗንም አውስተዋል፡፡

በመሆኑም ከሀገራት ያላት ግንኙነት ዘመን ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን የባለ ብዙ ወገን ማለትም የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት መስራች ሀገር ፤ የበርካታ ዓለም አቀፍ ሰነዶች ስምምነቶች የመጀመሪያ ፈራሚዎች ሀገራት መካከል ያለች ሀገር ናት ብለዋል፡፡

ታሪክ በጎም መጥፎም ነገሮችን ይመዘግባል ፤ ወደድንም ጠላንም ከታሪካችን ጋር መጋፈጥ ብቻ ሣይሆን መማር አለብን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን ቦታ ለማግኘትና ለመደመጥም አስቀድመን የጋራ ቤታችንን ማስተካከል ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ትውልዶች የሚጠበቅባቸውን አሻራ ማሳረፍ እንድለባቸው ጠቁመው÷ዲፕሎማሲያችን ከወቅቱ ጋር የሚራመድ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደሚገባት እንድታድግ ለማድረግ ዲፕሎማሲያችን መሰናክሎችን አልፎ ወደ21ኛው ክፍለ ዘመን እየገባ እንደሆነ የሚያሳዩ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቅሰው ፥ በዚህም ብዙ ስራ ይጠብቀናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ያለፉት ሦስት ዓመታትን ጨምሮ ብዙ ውጣውረድን ያለፈ እንደሆነ አንስተው ፥ ዛሬ በሚጀምረው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሣምንት ደግሞ ብዙ ሊያስተምረን ይችላል ነው ያሉት፡፡

አውደ ርዕዩን በመጎብኘትም የሀገራቸውን የዲፕሎማሲ ታሪክ ተረድተው ለሀገር የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆኑም ባለድርሻ አካላትን አደራ ብለዋል፡፡

ወጣት ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ ስራ ለመሰማራት አስፈላጊውን ትምህርትና ክህሎት ለማግኘት እንዲነሳሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

Exit mobile version