የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች 121 ሚሊየን ብር የሚገመት ምግብና አልባሳት ተበረከተ

By Meseret Awoke

January 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች 121 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡

ድጋፉን ያበረከቱት የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ድጋፉን የተቋማቱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ዛሬ በመቀሌ በመገኘት ነው ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያስረከቡት።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ÷ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፉ ይቀጥላል ብለዋል።፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር ) በበኩላቸው እንዳሉት ÷ በሰው ሰራሽ ችግር ዋና ተጠቂ የሚሆኑት ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትብብር መሰራት አለብን፡፡

የጉምሩክ ከሚሽነር ደበሌ ቃበታ ÷ በጋራ የተደረገው ድጋፍ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች 121 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ምግብና የተለያዩ አልባሳት መሆኑን ጠቁመዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ረዳ ÷ የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች መምጣታቸው እና ድጋፍ ማድረጋቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

አቶ ጌታቸው ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡