የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል በሁለት ቢሊየን ብር ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው

By Shambel Mihret

January 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በትግራይ ክልል በሁለት ቢሊየን ብር ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሻሻያ ፕሮጀክት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግርማይ ግደይ እንደገለጹት÷ በፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚያሻሽሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

በክልሉ በእንጨት ምሰሶዎች መውደቅና በትራንስፎርመሮች መቃጠል ሳቢያ የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ ለመከላከል ይረዳልም ብለዋል።

በዚህም በኃይል ማስተላለፊያነት ያገለግሉ የነበሩ የእንጨት ምሰሶዎች በኮንክሪት እየተቀየሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ ትራንስፎርመሮችን መጠገንና መቀየርን እንደሚያካትትም አቶ ግርማይ አብራርተዋል።

በፕሮጀክቱ በ14 ማህበራት የተደራጁ 1 ሺህ 500 ወጣቶች ሥራ እንደተፈጠረላቸውም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዲስትሪክቱ ከፍተኛ መሐንዲስ ኢንጂነር አብርሃም ከበደ÷ በ950 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኙ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት እየተቀየሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም ሥራው 90 በመቶ መከናወኑን በመግለጽ እየተቀየሩ ያሉት ምሰሶዎች ከ30 እስከ 40 ዓመታት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችሉም አብራርተዋል።