ዓለምአቀፋዊ ዜና

የፀጥታው ምክር ቤት የሁቲ አማጺያን በቀይ ባህር የሚፈፅሙትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጠየቀ

By Meseret Awoke

January 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የሁቲ አማጺያን በቀይ ባህር የሚፈፅሙትን ጥቃት እንዲያቆሙ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ አፅድቋል፡፡

አማፂያኑ ጥቃት እንዲያቆሙ የሚጠይቀው የውሳኔ ሃሳብ በጃፓን እና አሜሪካ የቀረበ ሲሆን በ11 ድምፅ ያለምንም ተቃውሞ እንዲሁም በአራት ድምፅ ተዓቅቦ ፀድቋል፡፡

በተጨማሪም በፀጥታው ምክር ቤት የሁቲ አማጽያንን ትደግፋለች የተባለችው ኢራን በምክር ቤቱ እንደትወገዝ ተጠይቋል፡፡

የውሳኔ ሃሳቡ የሁቲ አማጺያን በትላንትናው እለት በአሜሪካ መርከቦች ላይ የፈፀሙትን ከበድ ያለ ጥቃት ተከትሎ የቀረበ ሲሆን ምክር ቤቱ ጥቃቱ የዓለም የንግድና የመርከቦችን እንቅስቃሴን የሚያደናቅፍና የሚገታ ነው ሲል አውግዞታል፡፡

በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የሁቲ አማፂያን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና ከነበረው የየመን መንግስት ጋር የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የገቡ ሲሆን ሰሜናዊ የመንን ተቆጣጥረው ይገኛሉ፡፡

አማፂያኑ እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈፅመውን የአየር ጥቃት ተከትሎ በቀይ ባህር ለእስራኤል ድጋፍ ሰጭ ናቸው ባሏቸው የአሜሪካ እና የሌሎች ሀገራት መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡

ጥቃቱን ለመከላከል እና የቀይ ባህር ደህንነትን ለመጠበቅ አሜሪካ መራሽ ጥምረት ሀይል የተቋቋመ ቢሆንም የአማፂያኑ ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡