አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ በጀረር ዞን ደገሀቡር ከተማ አስተዳደር እየተካሄዱ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የሥራ ሂደት ተመልክተዋል።
በጉብኝታቸውም ግንባታቸው እየተከናወኑ የሚገኙ 4 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የመንገድ ፣ የደገሀቡር ሆስፒታልን የማስፋፊያ፣ የደገሀቡር ከተማ እስታዲየም እና የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደትን ተመልክተዋል፡፡
የመንገዶቹ ግንባታ እየተከናወነ የሚገኘው በከተማ ልማትና ግንባታ ቢሮ እንዲሁም በደገሀቡር ከተማ አስተዳደር አማካኝነት መሆኑን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡
የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን የማገልገል አቅም እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከጉብኝታቸው በኋላ ከከተማዋ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸው ተመላክቷል፡፡