አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ለብዙ ዓመታት ማገልገል እንዲችል ታሳቢ ተደርጎ በቀጣይ የሚጸድቅ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
በዛሬው ዕለት በግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ ይፋዊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን÷ በመድረኩ በኢትዮጵያ የግል ዳታ ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገልጿል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በውይይቱ÷ የግል ዳታ ጥበቃ አዋጁ መውጣት በቀጣይ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ረቂቅ አዋጁ ለረጅም ጊዜ እንዲያገልግ እና የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ በቀጣይ በምክር ቤቱ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሕግ ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አያልነህ ለማ የግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ባቀረቡበት ማብራሪያ÷ በቴክኖሎጂው እድገት ዓለም እየተቀያየረች በመሆኑ የግል ዳታዎች ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ለአንድ ጉዳይ የተሰበሰበ ዳታ ለሌላ ጉዳይ ስራ ላይ እንዳይውል ረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ማስቀመጡንም መግለጻቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢ/ር)÷ የግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ በባለስልጣኑ ስር እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት ከአስፈጻሚ አካላት ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ስራውን ማከናወን እንዲችል ነው ብለዋል፡፡