አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ዲፕሎማሲ ለብሔራዊ ጥቅማችን” በሚል የሚካሄደው የዲፕሎማሲ ሣምንት ዓውደ-ርዕይ በነገው ዕለት በይፋ እንደሚከፈት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) ዓውደ ርዕዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር የሁሉም ሕብረተሰብ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
አምባሳደር መለስ (ዶ/ር)÷ “ዲፕሎማሲያችን ከአፍሪካ መዲናነት እስከ ዓለም ዓቀፍ መድረክነት” በሚል ሥያሜ በሚካሄደው ዓውደ-ርዕይ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ በመዲናይቱ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡
ዘመናችን የደረሰበት የዲፕሎማሲ አካሄድ በዲጂታሉ ዘርፍ እየታገዘ በመሆኑ ኢትዮጵያም ራሷን እያዘመነች እንደምትጓዝና በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገሩ አምባሳደር እንዲሆን በዲፕሎማሲው ሳምንት ቃል የሚገባበት እንደሚሆንም ገልጸዋል።
በሳይንስ ሙዚየም የሚካሄደው ዓውደ-ርዕዩ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ከማፅናት አንፃር ዐቅም የሚፈጥር እንደሆነ ተነግሯል።
ለሦስት ሣምንታት በሚቆየው መርሐ ግብር÷ የፓናል ውይይት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የ116 ዓመታት ጉዞ የሚያሳይ መፅሐፍ ለአንባቢያን መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ሥድስት ጥናታዊ ፅሑፎች እንደሚቀርቡና ዲፕሎማቶችን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድርም ይካሄዳል ተብሏል፡፡
ዓውደ ርዕዩ÷ ኢትዮጵያ ከመንግሥታቱ ማኀበር እስከ ብሪክስ አባልነት የተጓዘችበትን የዲፕሎማሲ መንገድንም እንደሚያሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በታሪኩ ወልደሰንበት