አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቶግ የተባለው የቱርክ ኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ ሁለተኛ ሞዴል መኪና ይፋ አድርጓል፡፡
በሀገር ውስጥ የተመረተው ሁለተኛው ሞዴል መኪና “T10F” የሚል የምርት መለያ የተሰጠው ሲሆን ÷በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት በአሜሪካ ላስ ቬጋስ በሚካሄደው አለምአቀፉ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ላይ ለእይታ ይቀርባል ተብሏል፡፡
የቶግ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ መህመት ጉርካን ካራካስ÷ ሁለተኛው ሞዴል የኤሌክትሪክ መኪና ለኩባንያው አዲስ ምዕራፍን የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡
መኪናውን ለመገጣጠም ከአምስት አመት ከግማሽ በላይ መፍጀቱን ያመላከቱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ÷ ቱርካውያን ከዚህ በኋላ በሀገራቸው የተገጣጠመውን መኪና ይነዳሉ ነው ያሉት፡፡
ቶግ ኩባንያ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በዓመት ከ200 ሺህ በላይ የቱርክ መኪናዎችን ወደውጭ ለመላክ ማቀዱ የተገለፀ ሲሆን÷ በ2030 ከ1ሚሊየን በላይ መኪናዎችን ወደ አውሮፓ ገበያ ያቀርባል ተብሏል፡፡
ኩባንያው የመጀመሪያውን ሞዴል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በህዳር ወር 2019 ይፋ አድርጎ እንደነበር ቲ አር ቲ ዎርልድ ዘግቧል፡: