Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ግለሰብ አግተው በገመድ በማሰር ቤተሰብ 300 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ሲያስፈራሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድን ግለሰብ አግተው እጅና እግሩን በገመድ በማሰር ቤተሰቡ 300 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍል ሲያስፈራሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሰረተ።

በፍትህ ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ባንተይደር ደርሶ እና ልዑል ጫላ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 586 እና አንቀጽ 590 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ዝርዝር ክስ ቀርቦባቸዋል።

በክስ ዝርዝሩ እንደተመላከተው፤ በታህሳስ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 3:00 ሰዓት ገደማ በለሚኩራ ክ/ከ ወረዳ 9 ጎሮ መስጂድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኤርትራ ዜግነት ያለው  መብርሐቱ ፀጋዬ የተባለ የግል ተበዳይን 1ኛ ተከሳሽ የወንድሜ ቤት ደርሰን እንምጣ በማለት በማታለል ወደ የካ አባዶ ጂ ሰቨን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በመውሰድ ባለሁለት ክፍል ቤት ውስጥ እንዲገባ ከደረገው በኋላ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የግል ተበዳዩን ከኋላው አንገቱ ስር ቢላ በመሰንዘር እንዳይንቀሳቀስ በማስፈራራት እጅና እግሩን ከወንበር ጋር በማሰርና አፉን አፍነዋል።

ከዚህም በኋላ 2ኛ ተከሳሽ በቢላዋ ፊቱንና ግንባሩን በመወጋጋትና በፒንሳ ፊቱን በመቆንጠጥ ሲያሰቃዩት እንደነበር በክሱ ላይ የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ፤ 1ኛ ተከሳሽ ከግል ተበዳይ ኪስ ውስጥ ስልክ በማውጣት በ2ኛ ተከሳሽ የሚፈጸመውን የማንገላታት እና የማስፈራሪያ ድርጊትን በስልክ በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረጽ በቴሌግራም ለግል ተበዳይ አክስት እንድትመለከተው በመላክ 300 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ካልላኩ እንገለዋለን በማለት ሲያስፈራሩ እንደነበረና የግል ተበዳዩ ድረሱልኝ አድኑኝ ብሎ እንዲነግራቸው በማዘዝ ሲያስፈራሩት እንደነበር ጠቅሷል።

በተጨማሪም በቴሌግራም፣ በዋትስአፕ እና በኢሞ ከወላጅ አባቱ ጋር በማገናኘትና ስልክ በመደወል ጭምር ገንዘቡን እንዲከፍሉ ሲደራደሩ እንደነበርም ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።

በዚህ መልኩ ተከሳሾቹ የግል ተበዳይን አግተው እያስፈራሩ ቤተሰቦቹ ገንዘብ እንዲከፍሉ በስልክ ሲደራደሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጋር ባደረጉት ክትትል እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ ሰውን የመጥለፍ ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ተከሳሾቹ ጠበቃ የማቆም አቅም እንደሌላቸው ጠቅሰው ቃለ መሃላ መፈጸማቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከተከላካይ ጠበቃ ጋር ተማክረው እንዲቀርቡም ለጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version