አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባበ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ ሰራተኞች የተሰጠው የቴክኒክና ባህሪ ብቃት ፈተና ውጤት ይፋ ሆኗል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው እና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች የተሰጠው ፈተና ውጤትን በሚመለከት መግለጫ ተሰጥቷል።
በመግለጫውም ታህሳስ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ለከተማ አስተዳደሩ አመራር፣ ባለሙያ እና ሰራተኞች የተሰጠውን የቴክኒክና ባህሪ ብቃት ፈተና የወሰዱት የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች ቁጥር 15 ሺህ 151 መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከዚሁ አጠቃላይ ቁጥር ለፈተና ከተቀመጡ 10 ሺህ 257 ፈፃሚዎች 5 ሺህ 95 ወይም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የማለፊያ ውጤት እንዳስመዘገቡ ተጠቁሟል፡፡
ቀሪ 50 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የተቀመጠውን የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገብ አለመቻላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
መመዘኛ ፈተናውን የወሰዱ ዳይሬክተር እና ቡድን መሪዎች ቁጥር 4 ሺህ 213 ሲሆን÷ የፈተውን ማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 34 በመቶ ወይም 1 ሺህ 422 የሚሆኑት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለፈተና ከተቀመጡት አጠቃላይ ቁጥር 681 የሚሆኑት በተለያየ የሥነ ምግባር ጥሰት ከፈተና ውጪ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
441 የሚሆኑት ደግሞ በፈተና ስፍራ ያልተገኙ መሆኑን ሃላፊው መናገራቸውን የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡