Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት አቋረጡ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት እያቋረጡ መሆኑን አስታወቁ።

የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ የዓለም ጤና ድርጅት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ቻይናን ተጠያቂ አላደረገም ከሚል የመነጨ ነው ተብሏል።

ፕሬዚዳንቱ ቻይና ድርጅቱ ላይ ጫና እያሳረፈችና እየተቆጣጠረችው ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

ትራምፕ በኋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ “ዛሬ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያለንን ግንኙነት እናቋርጣለን” ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ለድርጅቱ ይደረገ የነበረውን ድጋፍ ወደ ሌሎች አካላት እናዞረዋለንም ነው ያሉት።

የዓለም ጤና ድርጅትንም “የቻይና አሻንጉሊት” ሲሉ ወርፈውታል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የዓለም ጤና ድርጅት ያለው ነገር ባይኖርም ከዚህ ቀደም በትራምፕ ይቀርብበት የነበረውን ውንጀላ ሲያጣጥል ቆይቷል።

ቻይና በበኩሏ ከዚህ ቀደም አሜሪካ በራሷ ስህተት ለኮሮና ቫይረስ መጋለጧን ስትገልጽ ቆይታለች።

ዋሽንግተን የራሷን ስህተት በመሸፈንና ቻይናን በመኮነን ማካካሽ ትፈልጋለች ስትልም ትወቅሳለች።

አሜሪካ ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በየአመቱ ከፍተኛውን ገንዘብ ስትሸፍን ቆይታለች።

ቻይና በበኩሏ የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚያደርገው ጥረት 2 ቢሊየን ዶላር እንደምትሰጥ ቃል መግባቷ ይታወሳል።

የአሁኑ የትራምፕ ውሳኔ ከመቸ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ግን የታወቀ ነገር የለም።

አሜሪካ በፈረንጆቹ 1948 የተቀላቀለችውን ዓለም አቀፍ ተቋም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አሳውቃ የመውጣት መብት እንዳላት በሃገሪቱ ኮንግረስ ስምምነት የተደረሰበት የውሳኔ ሃሳብ ያመላክታል።

ምንጭ፦ ሬውተርስ እና ቢቢሲ

Exit mobile version