ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሃማስ ከሰሜን ጋዛ መወገዱን እስራኤል አስታወቀች

By Melaku Gedif

January 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃማስ ከሰሜን ጋዛ መወገዱን የእስራኤል መከላካያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ እንዳሉት÷ በጋዛ ሰርጥ በሚገኙ የሃማስ ይዞታዎች ላይ የሚወሰደው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡፡

አሁን ላይም በሰሜን ጋዛ የነበሩት በርካታ የሃማስ ታጣቂ ቡድን አባላት መወገዳቸውን ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይም በማዕከላዊ እና ደቡብ ጋዛ በመሸገው የሃማስ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል፡፡

በእነዚህ ቀጣናዎች ልዩ ዘመቻ እንደሚካሄድ ጠቁመው ÷ጦርነቱን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

በማዕከላዊ እና ደቡብ ጋዛ የሚገኙ የሃማሰ ታጣቂዎች በርካታ ከመሆናቸው ባለፈ የመሬት ውስጥ ዋሻ እና ሌሎች ወታደራዊ ስልቶችን እንደሚጠቀሙ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፍልስጤማውያን ጋዛ ለቀው ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ የሚደረገውን ግፊት ኮንነዋል፡፡

ሚኒስትሩ ጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ ጫና ሊደረገባቸው እደማይገባ እና የተፈናቀሉትም ሰላም ሲመጣ ወደ ቤታቸው ሊመሰሉ ይገባል ብለዋል፡፡

በሃማስ እና እስራኤል መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት እስካሁን በጋዛ ከ23 ሺህ በላይ ዜጎች ለሕልፈት መዳረጋቸውን ዘ ጋርዲያን የሆስፒታል ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡