አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው መስከረም ወር በሊቢያ ደርና ከተማ በጎርፍ አደጋ የፈረሱት ግድቦች ደካማ እንደነበሩ የዳኝነት ምርመራ ውጤት አመላከተ።
የሊቢያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አል-ሲዲቅ አል-ሱር በትናንትናው ዕለት እንደተናገሩት፤ በግድቡ ግምገማ ወቅት ቢያንስ 25 ባለሙያዎች ግዴለሽ መሆናቸው ለአደጋው መከሰት ምክንያት ሆኗል።
ከፈረንጆቹ 2003 ጀምሮ እነዚህን ግድቦች ለመጠገን እና ሶስተኛውን ግድብ ለመገንባት የቀረበው ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ አደጋውን ማስቀረት ይቻል እንደነበር በውጤቱ ተመላክቷል።
በፈረንጆቹ መስከረም 10 እና 11 የደረሰው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ የሊቢያ ሰሜን ምስራቅ ከተማ የሆነችውን ደርና ከተማን ማውደሙ ይታወሳል፡፡
አደጋውንም ተከትሎ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጎርፉ ጎረቤት አካባቢዎችንም መንካቱንና ወሳኝ የፍሳሽ እና የውሃ መሠረተ ልማቶችን ማውደሙን የገለፀ ሲሆን በወቅቱ አብዛኛውን ሞት ማስቀረት ይቻል እንደነበርም አመላክቷል፡፡
በደርና ከ 30 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉና ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችም በጎርፍ መጎዳታቸውን የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) መግለጹን አፍሪካ ኒውስ በዘገባው ጠቁሟል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!