ቴክ

ቻይና አነስተኛ የኤሌክትሪክ አውሮፕላን የመጀመሪያ የሙከራ በረራን በተሳካ ሁኔታ አከናወነች

By Meseret Awoke

January 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና አነስተኛ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ አውሮፕላን የመጀመሪያ የሙከራ በረራን በተሳካ ሁኔታ ማከናወኗ ተሰምቷል፡፡

ሁለት ሰው ማሳፈር የሚችለው እና ባለ አንድ ሞተሩ አነስተኛ የኤሌክትሪክ አውሮፕላን በበቻይና ሀገር መሰራቱ ተገልጿል፡፡

በቻይና አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ጄኔራል አውሮፕላን ኮርፖሬሽን የተሰራው ኤጂ60 ኢ አውሮፕላን በምስራቅ ቻይና ዠጂያንግ ግዛት ከሚገኘው ጂያንዴ ኪያንዳኦሁ አውሮፕላን ማረፊያ መነሳቱ ተመላክቷል፡፡

አጭር የሙከራ በረራ ካደረገ በኋላም እዚያው የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ ማረፉን ቻይና ዴይሊ አምራቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ኤጂ60 ኢ ኤሌክትሪካል በመሆን የተሻሻለው ኤጂ60 ሲሆን ፥ ሙሉ ብረት፣ ጎን ለጎን ባለ ሁለት መቀመጫ፣ አንድ ሞተር፣ ቀላል ክብደት ያለው አነስተኛ አውሮፕላን መሆኑ ነው የተገለጸው።

ኤጂ60 የተነደፈው እንደ በረራ ስልጠና፣ የግብርና ዳሰሳ እና የአየር ላይ ጉብኝት ዓላማ እንደነበር ተገልጿል።

የኤሌክትሪክ አውሮፕላኖች በተለምዶ በሚሞሉ ሊቲየም-አዮን ባትሪዎች እና ዜሮ-ካርቦን ልቀት የኤሌክትሪክ ሞተሮች እንደተገጠሙላቸው አርቲ ዘግቧል፡፡

የኤሌክትሪክ አነስተኛ አውሮፕላኖች በሌሎች ሀገራት የተሰሩ ሲሆን ፥ በእስራኤል ኢቪዬሽን የተሰራው በዓለም የመጀመሪያው ሙሉ የኤሌክትሪክ አውሮፕላን ነው፡፡

የአውሮፓውያንን ኤርባስ ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች የኤሌክትሪክ አውሮፕላኖችን ለማምረት ሽር ጉድ እያሉ እንደሚገኙም በዘገባው ተጠቁሟል፡፡