Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የሃይማኖት አባቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የገና በዓልን በማስመልከት የ’እንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው÷ የኢየሱስ ክርስቶስ ውልደት የሠላም፣ የትህትናና የፍቅር ማሳያ ነው፤ በዓሉን ስናከብርም ይህንኑ በማሰብ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በዓሉን ሲከበር÷ በድርቅና በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን በማሰብና በመጠየቅ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ በበኩላቸው÷ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ፣ ሰማይ እና ምድርን ለማስታረቅ እንደ ሰው ሥጋን ለብሷል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ከራስ ወዳድነት ወጥተን የተራቡ፣ የታረዙና የተጠሙትን በማሰብ፤ የተበደሉ፣ የታመሙና የተፈናቀሉትን በማስታወስ፤ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ውስጥ ለገቡ ወገኖች አለኝታ በመሆን ሊሆን እንዲገባ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ (ዶ/ር)÷ በዓሉ ሲከበር እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያሳየውን ፍቅርና ወደር የሌለው ቸር ሥጦታውን እያሰቡ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን እንዲሁም አቅመ ደካሞችን በማሰብ እንዲከብርም ጠይቀዋል፡፡

በቤተልሔም መኳንንት እና ማሕሌት ተክለብርሐን

Exit mobile version