አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የላንሴት አጠቃላይ ሆስፒታል ሰራተኞች የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ የደም ልገሳ መርሐ ግብር አካሂደዋል፡፡
የላንሴት አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሄኖክ ሰይፈ÷ ሆስፒታሉ በዘርፉ የካበተ ልምድ እና ብቃት ባላቸው ስፔሺያሊስት ሐኪሞች የተሟላ የጤና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዓለም የደረሰበትን የሕክምና ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት ቀልጣፋ እና አስተማማኝ እንዲሁም ሕብረተሰቡን ያማከለ አገልግሎት ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
በዚህም ዘመኑን የዋጀ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ለህክምና የሚደረገውን የውጪ ሀገር ጉዞ እና እንግልት ለማስቀረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የላንሴት አጠቃላይ ሆስፒታል ማህበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም ከባለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም የሆስፒታሉን ሰራተኞች እና ነዋሪችን በማስተባበር በህክምና ሥራ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የደም ልገሳ መርሐ ግብር ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡
ደም መለገስ የሌሎችን ሕይወት መታደግ ነው የሚሉት ዶክተር ሄኖክ÷ ሕብረተሰቡ ደም መለገስን ቋሚ ልምድ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በደም ልገሳ መርሐ ግብሩ የተሳተፉት የሆስፒታሉ ሰራተኞች በበኩላቸው÷ የሰውን ሕይወት ለማስቀጠል ደም በመለገሳቸው መደሰታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በሆስፒታሎች የደም እጥረት በስፋት እንደሚያጋጥም ጠቁመው÷ ዜጎች ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ