Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሩሲያ በወታደራዊ ሀይሏ ውስጥ ለሚገኙ የውጭ ሀገራት ዜጎች ዜግነት ልትሰጥ ነው

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 26 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያ ጦር ውስጥ የሚገኙ የውጭ ሀገራት ዜጎች የሩሲያ ዜግነት እንደሚሰጣቸው ክሬምሊን አስታውቋል፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሀገሪቱ ጦር ወይም በሌሎች ወታደራዊ ክፍሎች ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች የሩሲያን ፓስፖርት እንዲያገኙ ሚያስችለውን የውሳኔ ሃሳብ ፈርመው ማፅደቃቸው ተገልጿል፡፡

በውሳኔ ሃሳቡ መሰረት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ወቅት በሩሲያ መከላከያ ሃይል ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ የውጭ ሀገራት ዜጎች ቤተሰቦችም የሩሲያ ዜግነት የማግኘት መብት አላቸው ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት በጤና ምክንያት ከውትድርና የተሰናበቱ እንዲሁም በጡረታ የተገለሉ እና የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የጦሩ አባላት የዜግነት መብት የሚያገኙ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም የሩሲያ ጦር አባል የሆኑ የውጭ ሀገራት ዜጎች አስፈላጊውን ማስረጃ አሟልተው ከተገኙ በአንድ ወር ውስጥ የሩሲያ ዜግነት ጥያቄያቸው ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል፡፡

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተከሰተ በኋላ በዩክሬን በኩል ከ13 ሺህ 500 በላይ የሌላ ሀገር ወታደሮች መሰለፋቸው ይነገራል።

በተመሳሳይ በሩሲያ ጦር ትክክለኛ ቁጥሩ ባይታወቅም በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች በወታደርነት ማገልገላቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version