አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የትምሕርት ሥርዓት ተማሪዎችን ከሌላው ዓለም ጋር መወዳደር እንዲችሉ የሚያስችል ሆኖ መቀረፅ እንዳለበት ትምሕርት ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
ትምሕርት ሚኒስቴር “በትምሕርት ሥርዓታችን ምን ዓይነት ትውልድ እንገንባ” በሚል ርዕስ ከትምሕርት አማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይቷል፡፡
የትምሕርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)÷ በኢትዮጵያ ያለው የትምሕርት ሥርዓት ችሎታ፣ ዕውቀት፣ ክኅሎት፣ ግብረ-ገብነትና ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች እንዲያፈራ መሥራት ያሥፈልጋል ብለዋል፡፡
እስከ አሁን በነበረው የፈተና ሥርዓት በ12ኛ ክፍል የማጠቃለያ ፈተና ተማሪው ምን ያህል ዕውቀት አለው የሚለውን የሚለካና 12ኛ ክፍል ለማጠናቀቅ ወይም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያበቃ መሆን አለመሆኑን መፈተሽና በቀጣይ ማስተካከል እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ በትምሕርት ላይ በሚሠራው ሥራ መግባባትና በምክንያት የሚያምኑ ዜጎችን መፍጠር ቢቻል በሀገራችን የሚስተዋሉ ችግሮች አይፈጠሩም ነበር ብለዋል፡፡
ስለሆነም የትምሕርት ማኅበረሰቡና አመራሩ የትምሕርት ሥርዓቱን በመለወጥ ረገድ መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው ብለዋል።
የትምሕርት ሥርዓቱ ተማሪዎችን እንደ ፍላጎታቸውና ችሎታቸው ማስተናገድ የሚያስችል መሆን እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
በተለይ ለሣይንስ፣ ምህንድሥና፣ ቴክኖሎጂ እና ሒሳብ ትምህርቶች ልዩ ትኩረት በመሥጠት ዓለም አቀፍ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ተወዳዳሪ ዜጎችን ማብቃት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ሁሉንም ተማሪዎች በአንድ ቋት ውስጥ አስገብቶ ማስተማርና መፈተን እንደማይገባ ተናግረዋል።
ከፍተኛ ችሎታ፣ ብቃት፣ ዕውቀትና ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች የሚያወጣ ተቋም ለማፍራትም እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከሌላው ዓለም ጋር መወዳደር የሚችሉ ተማሪዎች እንዴት መፍጠር እንችላለን የሚለውን መመለስና ለዚህም መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ልዩ ተሠጥዖ ያላቸውን ተማሪዎች መለየትና ማፍራት ይገባል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡