አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስመር አጥቂው ሽመልስ በቀለ ከ15 ዓመታት በላይ የብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት በኋላ ራሱን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ይፋ አድርጓል።
የመስመር አጥቂው የእግር ኳስ ጅምሩን ሀዋሳ ከተማ ያደረገ ሲሆን÷ በኋላም በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታ አድርጎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ክብርን ከክለቡ ጋር አሳክቷል፡፡
ከሀገር ውጪም በሊቢያ ለአሊተሃድ እና ለሱዳኑ ኤልሜሪክ መጫወቱ የሚታወስ ነው፡፡
በቀጣይም ወደግብፅ በማቅናት ፔትሮጀክት ፣ ኤልጉና ፣ ማስሪ ኤልመካሳ እና ኤን ፒፒ አይ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡
ከአስር ዓመታት የውጪ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ በመመለስ መቻልን የተቀላቀለው ሽመልስ ÷15 ዓመታትን ካሳለፈበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡
ሽመልስ በብሔራዊ ቡድን ግልጋሎቱ 83 ጨዋታዎችን በማድረግ 16 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን÷ 13 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል መቻሉም ተመላክቷል፡፡