አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንክ የእስራዔል-ሃማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለ4ኛ ጊዜ በዛሬው እለት በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የእስራዔል እና ሃማስ ጦርነት ወደ ጎረቤት ሀገራት መስፋፋቱን ተከትሎ በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት ነው ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚያመሩት፡፡
በተለይም የሃማስ አመራሮች በሊባኖስ መገደላቸው እና በትናንትናው እለት በኢራን በተፈፀሙ ሁለት የቦንብ ጥቃቶች 103 ኢራናውያን መሞታቸውን ተከትሎ በቀጣናው ውጥረት መንገሱ ለብሊንከን ጉብኝት ዋና ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው በመጀመሪያ ወደ እስራዔል ቴልአቪቭ ያመራሉ የተባለ ሲሆን በዝርዝር ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት ግን የተገለፀ ነገር የለም፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር÷ የእስራዔል እና ሃማስ ጦርነት እየተስፋፋ መሆኑን ገልፀው፤ የግጭቱ መስፋፋት የአሜሪካም ሆነ የሌሎች ሀገራት ፍላጎት አይደለም ብለዋል፡፡
90 ቀናትን ባስቆጠረው የእስራዔል-ሃማስ ጦርነት እሰካሁን 22 ሺህ 313 ንፁኀን ፍልስጤማውያን ሕይዎታቸው ሲያልፍ ከ57 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን ቲ አር ቲ ዎርልድ ዘግቧል፡፡