የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ የባሕር በር በምታገኝበት የመግባቢያ ሥምምነት ዙሪያ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ምን አሉ?

By Alemayehu Geremew

January 02, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትናንትናው ዕለት ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን ሥምምነት ከሶማሊላንድ ጋር መፈራረሟን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛዎች ሥምምነቱን እና የባሕር በር ጥያቄን የተመለከቱ መረጃዎች አውጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎችም ሥምምነቱን የተመለከቱ መረጃዎች ይዘው ወጥተዋል፡፡

ለአብነት ቢቢሲ ይዞ በወጣው መረጃ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የምትችልበትን መንገድ እየጠረገች መሆኑን በርዕሱ አስነብቧል፡፡

ቢቢሲ በዘገባው የባሕር በር የሌላት ይህች ሀገር አንድ ቀን የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላትን የመጀመሪያ ሕጋዊ ሥምምነት ፈርማለች ብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ ነው ማለታቸውንም አስታውሷል፡፡

የቱርኩ አናዱሉ የዜና አገልግሎት÷ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የነበራትን ጉጉት ዕውን ለማድረግ እና የወደቦች ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ መንገድ ይጠርጋል ብሏል፡፡

የዜና ምንጩ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው ከ1961 እስከ 1991 የቀጠለው የኤርትራ የነፃነት ጥያቄ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ምላሽ ካገኘ በኋላ መሆኑንም አስታውሷል፡፡

የአሜሪካው ዘ ማሪታይም ኤክስኪዩቲቭ በበኩሉ÷ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷን የሚያመላክት መሆኑን በመግለጽ ጽፏል፡፡

ሥምምነቱም ሶማሊላንድ የባሕር ንግድ ምጣኔ ሐብቷን ለማሳደግ የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችላት አንድ አካል መሆኑንም ጠቁሞ፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተደረገ ስምምነት ስለመሆኑ ገልጿል።

ሶማሊላንድ የበርበራ ወደቧን በርካታ ኮንቴይነር የጫኑ መርከቦችን እንዲያስተናግድ አድርጋ እያዘጋጀችው መሆኑም ተመልክቷል፡፡