አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ ድጎማ መሰጠት ከተጀመረ ወዲህ እስከ ታኅሣስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ27 ቢሊየን ብር በላይ ለድጎማ ወጪ መደረጉን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
እንዲሁም ባለፉት ሥድስት ወራት÷ 1 ሚሊየን 151 ሺህ 503 ነጥብ 769 ሜትሪክ ቶን ነጭ ናፍጣ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ በቀለች ኩማ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም 426 ሺህ 113 ነጥብ 402 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙንም ጠቅሰዋል፡፡
ከነዳጅ ድጎማ ጋር በተያያዘም÷ ተሽከርካሪዎች ድጎማ ወስደው ሕብረተሰቡን በአግባቡ በተፈቀደ ታሪፍ መሠረት ያለማገልግል ችግር እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
በሕብረተሰቡ በኩልም ታሪፍን አውቆ መብትን በአግባቡ ያለመጠየቅ እና ችግር ሲያጋጥምም ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ያለመስጠት ውስንነቶች መኖራቸውን ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
በዮሐንስ ደርበው