አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት የሰሜን ሸዋ ዞን፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር እና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች በተገኙበት በደብረ ብርሃን ከተማ በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ መክሯል፡፡
የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ እና የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ÷ የሕዝብን ሠላም የሚያውኩ የፅንፈኛው ኃይል እና አሸባሪው ሸኔ አበላት መመታታቸውን ገልፀዋል፡፡
ውጤቱ የተገኘውም በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በሲቪል አመራሩና በሕዝቡ የተባበረ ክንድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ልዩነቶችን በኢትዮጵያዊ አስተሳሰሰብ በውይይት መፍታት እንደሚቻል ገልጸው÷ ሀገር ከሌለች ግን የሚፈታ ችግር እንደማይኖርም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ፅንፈኛው ኃይልም ሆነ አሸባሪው ሸኔ የሕዝቦች ቀንደኛ ጠላት በመሆናቸው÷እነዚህን ፀረ-ሕዝብ ኃይሎች እስከመጨረሻው ተከታትሎ ለማጥፋት የፀጥታ ኃይሉ፣ የአስተዳደር አመራሮች እና ሕዝባዊ ቅንጅታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቀይቀዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው÷ በተደረገው የሰላም ጥሪ እስካሁን 361 የፅንፈኛው ኃይል ታጣቂዎች እጃቸውን በሰላም መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዞኑ ተባባሪ የፀጥታ ኃይሎችን ከሰራዊቱ ጋር ሆኖ በማሰልጠን ወደ ስራ ማስገባቱን እና በዚህም አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም ነው ያስታወቁት፡፡
እንዲሁም የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት÷ ፅንፈኛው ኃይል ከጅምሩ ሕዝብን አሳስቶ እንደነበር እና አሁን ላይ ግን ሕዝቡ የዚህን ቡድን መሰሪ ተግባር ተረድቶ ከሠራዊቱ ጎን መሰለፉን ጠቅሰዋል፡፡
ከሠራዊቱና ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሰለፍም በአጭር ጊዜ የፅንፈኛ ቡድኑን ርዝራዥ ከዞኑ ለማፅዳት እየተሠራ ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡