የሀገር ውስጥ ዜና

የፈረንጆቹ 2023 የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት ይበልጥ የተጠናከረበት ነበር ተባለ

By Alemayehu Geremew

January 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያሳለፍነው ዓመት የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት በዘርፈ ብዙ ስትራቴጂያዊ ግንኙነቶች ተጠናክሮ የቀጠለበት ታሪካዊ ወቅት እንደነበረ ተገለጸ፡፡

ሀገራቱ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው በዐቅም ግንባታው ዘርፍ፣ በዕውቀት ሽግግር እንዲሁም በሕዝቦቻቸው የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥሮች ፍሬያማ ውጤት ማስመዝገባቸውንም ዥንዋ አስነብቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንጆቹ ጥቅምት 2023 በቻይና ያደረጉት ጉብኝትም የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረው ሲሆን፤ የሀገራቱ ግንኙነት በማንኛውም ተለዋዋጭ ዓለማቀፋዊ ሁኔታ ፀንቶ ወደ ሚቆይ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ተሸጋግሯል።

በኢትዮጵያ የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ መላኩ ሙሉዓለም÷ የፈረንጆቹ 2023 የኢትዮ- ቻይና ግንኙነት ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ የሚታወስ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ቻይና ያቀረበችውን “የቤልት ኤንድ ሮድ፣ የዓለም አቀፍ ደኅንነት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ልማት ኢኒሺየቲቭ” ለመተግበር የታየውን ቁርጠኝነትም አስምረውበታል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ፖሊሲ ፕሮፌሰር ቆስጠንጢኖስ ብሩኅተሥፋ÷ የኢትዮ ቻይና ግንኙነት በተግባር ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡

ዓመቱ ቻይና ለኢትዮጵያ ዕድገት ዕውን መሆን የበኩሏን የተወጣችበት እንደነበር አንስተው፤ የሀገራቱ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር በለው ደምሴ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ቻይናን ጨምሮ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር መሥራቷ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን ለማፋጠን እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሙከሪም ሚፍታህ ኢትዮጵያ በብሪክስ ተቀባይነት ማግኘቷ ከሀገራቱ ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ተቋማዊ ግንኙነት እና ትብብር እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በአብነትም የቻይናው ኮንፊሺየስ ተቋም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለነበረው የ10 ዓመታት ቆይታ ዕውቅና ማግኘቱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ ኮራ ጡሹኔ ÷ ተቋሙ የኢትዮ-ቻይናን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስና የሀገራቱን የቋንቋ ትምሕርት እና ባሕል በማስተዋወቅ ረገድ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንደነበረውም አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር የትብብር ማዕቀፍ ፣ በቻይና ትብብር የመጠቀችው የኢትዮጵያ ሳተላይት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በሪሞት ሴንሲንግ አተገባበር ፣ በኢንዱስትሪ፣ በመሠረተ-ልማት፣ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፎች እና በሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ስለነበራት ትብብርም ተነስቷል፡፡