የሀገር ውስጥ ዜና

በከተማዋ ጠጥተው በሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር ሊደረግ ነው

By Amele Demsew

January 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በከተማዋ ጠጥተው በሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር ሊደረግ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ ዘመናዊ የአልኮል መመርመሪያ መሳሪያዎችን በ7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግዢ ፈፅሞ በዛሬው ዕለት ለትራፊክ ፖሊስ ርክክብ ይደረጋል፡፡

ባለስልጣኑ ህግ በተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተጠናከረ ቁጥጥር በማድረግ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

በኢትዮጵያ አብዛኛው የትራፊክ አደጋ ጠጥቶ በማሽከርከር የሚከሰት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህንን ችግር ለመቀነስ ከመጠን በላይ ጠጥተው የሚያሽከረክሩ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የትንፋሽ ቁጥጥር ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ለዚህም በአዲስ አበባ ጠጥቶ በማሽከርከር ሳቢያ የሚደርሰውን የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትን ለመከላከል በከተማዋ በተመረጡ ቦታዎች የአሽከርካሪዎች የትንፋሽ ቁጥጥር በዚህ ሳምንት በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል ተገልጿል ።

በምንተስኖት ሙሉጌታ