ቢዝነስ

ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል ያለመ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

January 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል የጸረ- ኮንትሮባንድ የንቅናቄ መድረክ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ባዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ ላይም የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በመድኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ሰፊና ተደራራቢ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑም ኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ችግሩን በአግባቡ ለመከላከል የሚያስችሉ የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የንቅናቄ መድረኩ በተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ ሥራ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ኮንትሮባንድ የንግድ ሥርዓቱን በማዛባት፣ ገቢን በማሳጣት እና ኢንቨስትመንትን በማዳከም በሀገር ላይ ተደራራቢ ችግሮች እንደሚያስከትል አስገንዝበው፤ ችግሩን ለመፍታት በሕግ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት እና መላው ሕብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!