አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታ በሜዳቸው ያደረጉት ፉልሃምና ቶተንሃም ድል ቀናቸው።
አርሴናልን ያስተናገደው ፉልሃም በ29ኛውና በ59ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ከተመሪነት ተነስቶ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
የማሸነፊያ ጎሎቹን ሄሜኔዝ እና ዲ ኮርዶቫ-ሬይድ ሲያስቆጥሩ፤ የአርሴናልን ጎል ደግሞ ሳካ በአምስተኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።
በሌላኛው የ20ኛ ሳምንት ጨዋታ በርንማውዝን ያስተናገደው ቶተንሃም ሆትስፐር 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል።
የማሸነፊያ ጎሎቹን ሳር በዘጠነኛው፣ ሰን ሆንግ-ሚን በ71ኛው እንዲሁም ሪቻርልሰን በ80ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥሩ፤ በርንማውዝን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነውን ብቸኛ ጎል ስኮት በ84ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።