አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለጤና ከፍተኛ ጥቅም ከሚሠጡ አትክልትና ሥራሥር ተክሎች አንዱ ቀይ ሥር ነው፡፡
ቀይ ሥር በርካታ የጤና ጥቅሞች እንዳሉትም የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ከበርካታ ጥቅሞቹ መካከልም÷ ዕይታን ለማሻሻል፣ የጉበት ሥብን (ኮሌስትሮል) ለማስወገድ፣ የሆድ ድርቀትን ለማስወገድ፣ የደም ግፊትን ለመከላከል እና የሆድ ቁስለትን ለማስታገስ የሚሉትን ለአብነት ያነሳሉ፡፡
1. ዕይታን ለማሻሻል ፡- በተለይም ሰዎች ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ቀይ ሥር ቢመገቡ የዕይታቸውን ሁኔታ ባለበት ለመጠበቅ ብሎም ለማሻሻል እንደሚያግዝ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
2. የጉበት ሥብን ለማስወገድ ፡- የጉበት የሥብ መጠን ከሚፈለገው በላይ መሆን ውስብስብ የጤና ዕክሎችን እንደሚያስከትል ይታመናል፡፡
በመሆኑም ቀይ ሥር መመገብ የጉበትን ሥብ ለማስወገድ እና ጤናማነቱን ለመጠበቅ እንዲሁም ጉበታችን ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ ለማስቻል ይረዳል፡፡
3. የሆድ ድርቀትን ለማስወገድ ፡- በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር የምግብ መፈጨትን ለማፋጠን፣ ምግብ በሚመገቡበት ወቅትም ምቾት እንዲሰማና የሆድ ድርቀት እንዳያጋጥም ይረዳል፡፡
4. የደም ግፊትን ይከላከላል ፡- ቀይ ሥርን መመገብ ጤናማ የደም ዝውውር እንዲኖር ያስችላል ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ ይህም የልብ ሕመምን ጨምሮ በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ከመጋለጥ እንደሚታደግም ነው የሚገልጹት፡፡
5. የሆድ ቁስለትን ያስታግሳል ፡- ቀይ ሥር “ቤታላይን” በተሰኘ ንጥረ-ነገር የበለጸገ በመሆኑ የሰውነት ክፍሎችን ሥርዓት ለማስተካከል እንዲሁም የሆድ ቁስለትን ለማስወገድ ያግዛል መባሉን ኸልዝ ላይን አስነብቧል፡፡
አንድ 80 ግራም የሚመዝን ቀይ ሥር÷ 29 ኪሎ ካሎሪ፣ 1 ነጥብ 4 ግራም ፕሮቲን፣ 0 ነጥብ 1 ግራም ሥብ፣ 6 ነጥብ 1 ግራም ኃይል ሠጪ፣ 2 ነጥብ 1 ግራም ፋይበር፣ 304 ሚሊ ግራም ፖታሺየም እንዲሁም 120 ማይክሮ ግራም ፎሌት እንደሚይዝ መረጃው አመላክቷል፡፡