አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሕብረተሰቡን በማንቃትና ብርቱ ተሳትፎ በማድረግ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
ውይይቱ “ለሀገራዊ ምክክር እና ሀገራዊ መግባባት የኪነ-ጥበብ፣ የማስታወቂያ እና የሁነት ዝግጅት ተቋማትና ባለሙያዎች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕ/ር ) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለት ዓላማ ከግብ እንዲደርስ የሁሉንም ዜጋ እና ተቋማት ርብርብ የሚጠይቅ ነው ።
በተለይም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ዜጎች በአገራዊ ምክክሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ለዚህም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሚዲያን በመጠቀም ለሕዝብ ቅርብ የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡