Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሰላም ጥሪውን በማይቀበሉ ሃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል – መንግስት

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች በመጻረርና ሃብትና ንብረትን በማውደም የትኛውንም አይነት ጥያቄ መመለስ አይቻልም ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም÷ከውጪ እና ከውስጥ ተቀናጅተው በሃይል እና በጉልበት በብጥብጥ እና በአመጽ እኩይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን በሌሎች ላይ ለመጫን ብሎም ኢትዮጵያ ለማፍረስ የተቃጣውን ጥቃት የሀገራችን ሕዝቦች በማስተባበር በመመከት መቀልበሰ ተችሏል ብለዋል፡፡

አሁን ላይም በሀገሪቱ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

የሕዝብን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች እና መብቶች በመጻረር ሃብትና ንብረትን በማውደም የትኛውንም አይነት ጥያቄ መመለስ አይቻልም ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

የተለያዩ ጥያቄ እና ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ጥያቄዎቻቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲያራምዱና እንዲታገሉ የፖለቲካ ምህዳሩ ምቹ እንዲሆም መንግስት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ሰላምን ዘላቂ ለማድረግና ቂምን ለመሻር ከሒሳብ ማወረራድና የጥላቻ መንገድ መውጣት የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም አብራርተዋል፡፡

ካንዱ የታሪክ ምዕራፍ ወደ አንዱ ስንሸጋገር በይደር ያደሩ እና ያልተቋጩ ዛሬም አጨቃጫቂ የሆኑ ጉዳዮች ችግሩን ይበልጥ እያወሳሰቡት እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

በየአካባቢው ነፍጥ አንግበው ከተነሱ ሃይሎች ጋር የሀገሪቱ ሕገ-መንግስት በሚፈቅደውና የሀገር አንድነትን እና ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ የሰላም ውይይቶችን በማድረግ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመጡ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በአንጻሩ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያቀርበውን የሠላም ጥሪ በመግፋት ግጭትና ሁከት የሚፈጥሩ የጥፋት ሃይሎች ዛሬም መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

እነዚህ ሃይሎች መሰረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን የሚመልስ የፖለቲካ ሥልት እና አካሄድ የማይከተሉ እንዲሁም በሕዝብ ጥያቄ ሽፋን የሕዝብ መገልገያዎችን ማወደም የዕለት ተዕለት ተግባራቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ አውዳሚ እና እኩይ ድርጊታቸው የጸጥታ ሃይሎች ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው ከሚወስዱት እርምጃ ጋር ተዳምሮ ከሕዝቡ እንዲነጠሉ አድርጓቸዋል ብለዋል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፡፡

በቀጣይም መላው ሕዝብ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሰላምን ለመጠበቅ እና ለማጽናት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአሸባሪው ሸኔ ጋር መንግሥት የሠላም ንግግር ለማድረግ ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ጠቁመው÷ሠላምን ለማስጠበቅ ሲባል በሸኔ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም በርካታ የሸኔ አባላት ተደምስሰዋል ወይም እጅ ሰጥተዋል አሊያም የሎጂስቲክስ እና የሰብዓዊ ቀውስ እንዲደርስባቸው ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግስት በወሰደው አፋጣኝ እርምጃ ክልሉን ከመፍረስ አደጋ ከመታደግ ባለፈ የክልሉ የፖለቲካና አስተዳደር መዋቅር እንደ አዲስ እንዲደራጅ አድርጓል ብለዋል፡፡

በክልሉ ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎንም የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎም በርካታ ታጣቂዎች ወደ ተዘጋጀላቸው የተዋድሶ ማዕከላት እየገቡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አሁንም የሰላም ጥሪው ክፍት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ጥሪውን በማይቀበሉት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በኢኮኖሚ ዘርፍም መንግስት የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊስ ማሻሻያዎችን በማድረግ ኢኮኖሚውን የማነቃቃት ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመቅረፍም የትኩረት መስኮች ተለይተው ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

በአሁኑ ወቅት የመኸር አዝመራ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ተሰብስቦ በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version