የሀገር ውስጥ ዜና

ከውጭ የተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ መድረሱ ተገለጸ

By Amele Demsew

December 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለምርት ዘመኑ ከውጭ የተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለ2016/17 የምርት ዘመን ከውጭ ከገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ታህሳስ 20/2016 ዓ.ም ድረስ በዘጠኝ ዙሮች 4 ሚሊየን 380 ሺህ ኩንታል ጅቡቲ ወደብ መድረሱ ተመላክቷል፡፡

በዛሬው ዕለትም 550 ሺህ ኩንታል የኤን ፒ ኤስ እና ኤን ፒ ኤስ ቦሮን ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ጅቡቲ ወደብ መድረሷ ተገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎም ከውጪ የተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ወደ 4 ሚሊየን 380 ሺህ ኩንታል ከፍ ማለቱ ነው የተጠቆመው።

ከዚህ መጠን ውስጥ እስከአሁን 3 ሚሊየን 618 ሺህ 212 ኩንታል ማዳበሪያ ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው ተብሏል፡

ታኅሣስ 23፣ ጥር 7 እና ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም በሦስት መርከቦች ተጨማሪ 2 ሚሊየን 90 ሺህ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ፣ ኤን ፒ ኤስ ቦሮን እና ዩሪያ ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ እንደሚደርስ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡