የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 46 ሺህ 203 ሔክታር መሬት ከመጤ አረም ነጻ መደረጉ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

December 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ 46 ሺህ 203 ሔክታር መሬት ከመጤ አረም ነጻ ማድረጉን የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ ዕቅድ አፈጻጸሙን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡

በሩብ ዓመቱ 10 ሺህ ሄክታር መጤ አረም ዝርያዎችን ለማስወገድ ያቀደው ባለስልጣኑ ከዕቅድ በላይ ማሳካቱን በግምገማው ወቅት መመላከቱን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትግበራ ውጤታማነትን ለማሻሻል የሚያስችል የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቆጠራ የ10 ዓመት መነሻ ዕቅድም በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ተመልክቷል፡፡

የባለሥልጣኑ ኃላፊ አቶ ተሥፋሁን ዓለምነህ÷ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የደን ልማትና ጥበቃ፣ የአካባቢና ማኅበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ፣ የዱር እንስሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ላይ የተሰናዱ ሦስት መመሪያዎችን እንደገና ለማሻሻል የሚያስችል መረጃ የማሰባሰብና ረቂቅ የማዘጋጀት ሥራ መጠናቀቁ ተመልክቷል፡፡