የሀገር ውስጥ ዜና

ፓስፖርትና ቪዛ ለውጭ ዜጎች በመስጠትና ግለሰቦችን ወደ ውጭ በመላክ ወንጀል የተከሰሱ 36 ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ታዘዘ

By Alemayehu Geremew

December 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፓስፖርትና ቪዛ ለውጭ ሀገር ዜጎች በመስጠትና ሰነድ አልባ ግለሰቦችን ወደ ውጭ በመላክ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ 36 ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ተሰጠ።

ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1 ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

የቀድሞ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ግንበቶ ከዚህ በፊት በነበረ የስራ ድርሻቸው ምክንያት ጥቃት ሊፈጸምባቸው እንደሚችል መስጋታቸውን በመግለጽ በማረሚያ ቤት በልዩ ሁኔታ ከለላ እንዲደረግላቸው አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ትዕዛዝ እስኪሰጥበት ድረስ በፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ እንዲቆዩ ችሎቱ አዟል።

ሌሎች ተከሳሾችን በሚመለከት ግን ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ነው የታዘዘው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዘርፍ ዐቃቤ ሕግ ባሳለፍነው ረቡዕ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ በ60 ግለሰቦች ላይ በየደረጃው 15 የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ክሱ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል ቀደም ሲል በነበረ ቀጠሮ በዐቃቤ ሕግ በኩል 54ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰ ፈራኦል የተባለ ተከሳሽ ክሱ እንዲቋረጥለት በቀረበ ጥያቄ መሰረት መቋረጡ ይታወቃል።

ሌሎች ሁለት ተከሳሾች ደግሞ ማለትም የኢሚግሬሽን ዜግነት አገልግሎት የኬላዎች ዘርፍ ቡድን መሪ የነበረው 5ኛ ተከሳሽ አይክፋው ጓሳዬ ገረመው እና አለሚቱ የኔ አየሁ የተባለች 49ኛ ተከሳሽን በሚመመከት የቀረበባቸው የክስ ድንጋጌ ዋስትና የማያስከለክል መሆኑን ተከትሎ በ10 እና በ20 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ተፈተዋል።

በዛሬው ቀጠሮ በዋስ የተፈቱ ሁለት ግለሰቦች እና የቀድሞ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የምዝገባና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ግንበቶ አዋልሶ፣ የውጪ ዜጎች ቁጥጥርና ቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጅላሉ በድሩ፣ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቡድን አስተባባሪ ከድር ሰዒድ ስሩር፣ የኬላዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ቦጋለ ጨምሮ አጠቃላይ 39 ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል።

ቀሪ 20 ተከሳሾች ግን ችሎት አልቀረቡም።

ችሎቱ ባለፈው ቀጠሮ ክሱን በንባብ ካሰማ በኋላ ከ5ኛ፣ ከ13ኛ እና ከ37ኛ ተራ ቁጥር ከተጠቀሱ ተከሳሾች ውጪ ያሉ የሌሎች ተከሳሾች በጠበቆቻቸው በኩል ክሱ ግልጽ እንዳልሆነ ገልጸው ክርክሩ ከመቀጠሉ በፊት የክስ ግልጽነት ላይ ጥያቄ አለን በማለት አቤቱታ አቅርበው ነበር።

ፍርድ ቤቱም በቀረበው ጥያቄ ላይ ዐቃቤ ሕግ ለዛሬ መልስ እንዲያቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ባቀረበው የጽሁፍ መልስ የጠበቆቹ ጥያቄ ከክስ መቃወሚያ ጋር ተጠቃሎ መቅረብ እንዳለበት ጠቅሷል።

ለብቻው የግልጽነት ጥያቄ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ሊሰጥበት አይገባም የሚል መልስና በጉዳዩ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ወይም ትዕዛዝ ሊሰጥ ይገባል የሚል ከሆነ ደግሞ ክሱ መሰረታዊ ካልሆኑ የአሃዝ እና የስያሜ ስህተት ውጪ ግልጽ በመሆኑ ክሱ በቀረበበት አግባብ ሊቀጥል ይገባል በማለት ዐቃቤ ሕግ አስተያየት ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

እነዚህ በሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ሕግ ከተለያዩ ሀገራት ዜጎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ ከህግ ውጪ በጉቦ በዶላር እየተቀበሉ ለውጭ ዜጎች በመስጠት፣ ከህግ አሰራር ውጪ ቪዛ በመስጠት፣ ሰነድ አልባ ዜጎችኝ በጥቅም በህገወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት፣ መንግስት ላይ ጉዳት ማድረስ የሚሉ ነጥቦች በየተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በክስ ዝርዝሩ ተካቷል።

በታሪክ አዱኛ