Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሮማን አብራሞቪች በእስራኤል ባንክ የተጣለባቸው ማዕቀብ እንዲነሳ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያዊው ቢሊየነር ሮማን አብራሞቪች የእስራኤል ባንክ ሂሳባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ የጣለባቸው ማዕቀብ እንዲነሳላቸው ጠየቁ፡፡

የቀድሞው የቼልሲ ባለሀብት በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በተለያዩ ሀገራት ያላቸውን የገንዘብ ሂሳብ እንዳያንቀሳቅሱ በእንግሊዝ እና በአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ተጥሎባቸው ቆይቷል፡፡

ባለሀብቱ ከሰሞኑም በእስራኤል እና ሃማሰ ጦርነት የነፍስ አድን ስራ እያከናወነ ለሚገኘው ዛካ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ዝውውር ለማድረግ ያቀረቡትን ሃሳብ የእስራኤል ባንክ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ሚዝራህ ታፋሆት የተባለው ሶስተኛው የእስራኤል ግዙፍ ባንክ እንዳስታወቀው÷ ባለሀብቱ ገንዘቡን ለማስተላለፍ የፈለጉት የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ለመርዳት ሳይሆን እየተካሄደ ያለውን የእስራኤል እና ሃማስ ግጭት ለማባባስ ነው ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ሩሲያዊው ቢሊየነር በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት እስራኤል እና አሜሪካ ማዕቀብ እንዳልጣሉባቸው አስታውሰው፤ የእስራኤል ባንክ ሂሳባቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ ፈቃድ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የባለሃብቱን የገንዘብ ዝውውር ክልከላ ተከትሎም ዛካ የተባለው በጎ አድራጎት ድርጅት በእስራኤል ባንክ ላይ ክስ መመስረቱን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ከ30 ዓመታት በፊት የተመሰረተው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ፤ በተለያየ ጊዜ በጋዛ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሰብዓዊ ድጋፎችን እና የነፍስ አድን ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ተመላክቷል፡፡

Exit mobile version