አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አምሥት ወራት 131ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወጭ ንግድ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንዳሉት ÷ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን እየፈተኑት ያሉ ዓለማቀፋዊ ፣ አኅጉራዊና ሀገራዊ ችግሮች ቢኖሩም “የኢትዮጵ ታምርት” ንቅናቄ በፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር በበጀት ዓመቱ አምሥት ወራት ከዘርፉ 131 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
ቢሆንም ግን የተላኩ ምርቶች በመጠናቸው ልክ ተገቢውን ገቢ ማስገኘት አለመቻላቸውንም አስምረውበታል፡፡
በምክንያትነትም በኢትዮጵያ የአምራች ዘርፉ የዕሴት ጭማሪ ዝቅተኛ መሆን ከተላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ በተላከው ልክ እንዳይሆን ማድረጉንም ነው ያነሱት፡፡
ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም የአቅም አጠቃቀምን ከፍ ማድረግ ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደረጉ የድጋፍ ማዕቀፎችን ማሻሻልና በቅንጅት መሥራት አሥፈላጊ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው አምሥት ዘርፎች በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚቀመጥ ስለመሆኑም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡