አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ላይ የሚሳተፉ የማሕበረሰብ አባላትን ለመመልመል ከኦሮሚያ ክልል ሰባት ዞኖች፣ አራት ከተማ አስተዳዳሮች እና 109 ወረዳዎች ለተውጣጡ ተባባሪ አካላት በጅማ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
በስልጠና መድረኩ 791 ተባባሪ አካላት እየተሳተፉ እንደሆነ ተገልጿል።
በስልጠና መድረኩ አስተማማኝ ሠላም የሚረጋገጥበት የፖለቲካዊ እና የማሕበራዊ መደላድል እንዲመቻች የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በርካታ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋለውን አለመግባቶችን ለመፍታት ኮሚሽኑ በትኩረት እየሠራ ስለመሆኑም ተነግሯል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው ሥልጠና የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሲቪል ማሕበረሰቦች፣ አባገዳ እና አደ ሲንቄዎች፣ መምህራን፣ ዳኞች፣ የመንግሥት ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ግልጽ፣ ፍትኀዊ፣አካታች እና አሳታፊ ይሆን ዘንድም በምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን የመምረጥ ሂደቱ በጥንቃቄ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡
በወርቅአፈራው ያለው