የሀገር ውስጥ ዜና

ዳሸን ባንክና የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ አዲስ የዓየር ትራንስፖርት ክፍያ አገልግሎት ይፋ አደረጉ

By Alemayehu Geremew

December 28, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ደንበኞች የዓየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቅመው ክፍያ ቆይተው የሚከፍሉበትን አዲስ አማራጭ በጋራ አስተዋወቁ።

የዳሽን ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ዋና መኮንን አቶ ዮሐንስ ሚሊዮን እንደጠቆሙት÷ ‘ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል’ በሚል የተሰየመው ይህ አገልግሎት በደንበኞች ምርጫ መሠረት በ6 ወር ወይም በ12 ወር የብድር ክፍያ የሚሰጥ ነው፡፡

ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በዳሸን ባንክ የሂሳብ ቁጥር መክፈት እንደሚገባቸው እና በባንኩ ቢያንስ ለሦስት ወራት አገልግሎት ያገኙ መሆን እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ አክለውም ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት አቅራቢያቸው ወደሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በሚያመሩበት ወቅት አሥፈላጊ ሠነዶችን ማሟላት እንደሚገባቸው እና ማስያዣም ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ሥራ አሥፈፃሚ አቶ ለማ ያዴቻም÷ ዓየር መንገዱ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት ጋር ራሱን ለማጣጣም ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ከዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር ለደንበኞቻቸው ያቀረቡት አዲስ የክፍያ አማራጭም ተግባራዊ እንዲሆን የሞባይል መተግበሪያዎችን ከአዲሱ የክፍያ አገልግሎት ጋር የተቀናጀ እንዲሆን አድርገናል ብለዋል።

ብሔራዊ ዓየር መንገዱ እና ዳሽን ባንክ ወደፊትም የደንበኞችን አገልግሎት ለማዘመን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም በትብብር መሥራታቸውን ይቀጥላሉም ነው ያሉት።