Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአማራ ክልል መንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል መንግስት ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የገቡ ታጣቂዎች በዘጠኝ የተሃድሶ ማዕከላት ስልጠና መጀመራቸውን የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ከ700 በላይ ታጣቂዎች በጠዳ ተሃድሶ ማዕከል ዛሬ ስልጠና መውሰድ ጀምረዋል።

የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ በሪሁን መንግስቱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፥ በክልሉ የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር መንግስት በተደራጀ አግባብ ህግ የማስከበር ስራ እያከናወነ ነው።

እስካሁን በተከናወኑ ተግባራትም በየአካባቢው ሰላም በማስፈን የተሻለ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

ህግ ከማስከበር ስራው ጎን ለጎንም በተሳሳተ መንገድ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎችን በማወያየት ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል።

በዚህም የክልሉ መንግስት ያደረገውን ይፋዊ የሰላም ጥሪ የተቀበሉና የሰላም አማራጭ የተከተሉትን ወደ ህብረተሰቡ የመቀላቀል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡትን የተሃድሶ ስልጠና እንዳጠናቀቁ ሰላማዊ ህይወት የሚጀምሩበት ሁኔታ በአፋጣኝ የማመቻቸት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

በተሳሳተ መንገድ ችግር ወስጥ የገቡ ወገኖች ሰላማዊ አማራጭ እንዲከተሉ የሰላም ጥሪው እድል መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አላምረው አበራ ናቸው።

የተሃድሶ ሰልጣኞች በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል መርህ በመከተል ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የሰላም ጥሪውን ተቀብለውና በድርጊቱ ተፀፅተው የሚገቡ ወገኖች የበደሉትን ህብረተሰብ በልማት መካስ ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለአስር ቀናት በሚቆየው በዚህ የተሃድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት የክልልና የዞን አመራር አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

Exit mobile version