Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አደንዛዥ ዕጾችን ወደውጭ ሀገር ይዘው ሊወጡ የነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕግ የተከለከሉ አደንዛዥ ዕጾችን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ጊኒ ኮናክሪ እና ወደ ፊሊፒንስ ማኒላ ከተማ ይዘው ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ የውጭ ሀገር ዜጎች እስከ 7 ዓመት ከ8 ወራት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ፡፡

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ነው።

የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በተለያዩ ሁለት መዝገቦች እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል በሕግ ክልከላ የተደረገበትን ኮኬይን ዕጽ ማዘዋወር ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ ናይጄሪያዊው ናየሎ አቢና እና ሩሲያዊው ማኪዝም ዛይትሴቭ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በአንደኛውው መዝገብ በናየሎ አቢና ላይ ባቀረበው ክስ÷ ታኅሣስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም ከብራዚል ሳኦፖሎ በመነሳት የኢትዮጵያ ዓየር መንገድን በመጠቀም ወደ ጊኒ ኮናክሪ ከተማ ትራንዚት አድርጎ ሊሄድ ሲል ከምሽቱ 3:30 ላይ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተደረገ ፍተሻ በያዘው ሻንጣ ውስጥ 1 ሺህ 930 ነጥብ 67 ግራም ኮኬይን አደንዛዥ ዕፅ እንደተገኘበት ተመላክቷል፡፡

ዐቃቤ ሕግም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 525 ንዑስ ቁጥር 1 (ለ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት በግለሰቡ ላይ ክስ አቅርቧል፡፡

እንዲሁም ማኪዝም ዛይትሴቭ የተባለው ተከሳሽ ሚያዝያ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 5:30 ላይ የኢትዮጵያ ዓየር መንገድን ተጠቅሞ ወደ ፊሊፕንስ ማኒላ ከተማ ጉዞ ለማድረግ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እያለ በተደረገ ፍተሻ 5 ሺህ 119 ነጥብ 29 ግራም የኮኬይን ዕጽ ይዞ መገኘቱን ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ በማስፈር በተመሳሳይ ድንጋጌ ክስ አቅርቦበት ነበር።

ተከሳሾቹም በተለያየ ጊዜ በችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ÷ በችሎት ክሱን በንባብ በማሰማት አስተርጓሚ ተመድቦላቸው የክሱን ዝርዝር እንዲረዱ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትና የማያሰጥ መሆኑን ተከትሎም በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ከማረሚያ ቤት እየቀረቡ ጉዳያቸውን በጠበቆቻቸው አማካኝነት በችሎት ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

የቀረበባቸው የክስ ዝርዝር ላይም የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል መሰረት÷ ዐቃቤ ሕግ በተለያዩ ቀናት የሰውና የሠነድ ማስረጃዎችን ለችሎቱ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም በሁለቱም ተከሳሾች ላይ የቀረበውን ማስረጃ መርምሮ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም÷ ተከሳሾቹ ግን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቷል።

በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ናየሎ አቢና የወንጀል ሪከርድ እንደሌለው፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ጨምሮ አጠቃላይ ሦስት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በመካከለኛ የዕርከን ደረጃ በ5 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራትና በ4 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

ተከሳሽ ማኪዝም ዛይትሴቭ ደግሞ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ አለመኖሩን፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪና፣ የገጠመውን የጤና ዕክል ፍርድ ቤቱ የቅጣት ማቅለያ ይዞለት በመካከለኛ የዕርከን ደረጃ በ7 ዓመት ከ8 ወራት ጽኑ እስራትና በ4 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም በፍርድ ቤቱ የተጣለውን ቅጣት እንዲያስፈጽም ታዟል።

የይግባኝ መብታቸውም እንደተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version