የሀገር ውስጥ ዜና

ማኅበሩ 17 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው አምቡላንሶችን በድጋፍ አገኘ

By Amele Demsew

December 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሙሉ የሕክምና ቁሳቁስ የተሟላላቸው 17 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ሥድስት አምቡላንሶችን በድጋፍ አግኝቷል፡፡

አምቡላንሶቹ የተገዙት÷ በአውሮፓ ኅብረት ሲቪል ጥበቃና የሰብዓዊ ድርጅት እንዲሁም በኦስትሪያ ልማት ኤጀንሲ ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አራቱ አምቡላንሶች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ጎንደር እንዲሁም ሁለቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባምባሲ እና ዳንጉር አካባቢ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሏል።

የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ ጌታቸው ታዓ እንደገለጹት ÷ “ዛሬ ከተረከብናቸው አምቡላንሶች በተጨማሪ ለሚቀጥሉት 18 ወራት የ10 አምቡላንሶች የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች የሚሸፍን ድጋፍ ተደርጓል”።

በኢትዮጵያ የኦስትሪያ ቀይ መስቀል ተወካይ ተመስገን አበበ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንዳሉት÷ አምቡላንሶቹ ለ22 ሺህ 500 ሰዎች አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፡፡

በቅድስት አባተ