ጤና

የስትሮክ ምንነት?

By Amele Demsew

December 28, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስትሮክ የአንጎል የደም ሥሮች ደም የማዘዋወር ሥራቸውን ሲያቋርጡ ወይም በአንጎል ውስጥ ደም ሲፈስ የሚከሰት ድንገተኛና አደገኛ የሕመም ሁኔታ ነው።

ስትሮክ በገዳይነት ከሚታወቁት የህመም አይነቶች አንዱ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 15 ሚሊየን ሰዎች በስትሮክ እንደሚያዙ የሚገልጸው የዓለም ጤና ደርጅት መረጃ፤ አምስት ሚሊየን ሰዎች በዚሁ ሰበብ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሲሆን ሌሎች አምስት ሚሊየን ሰዎች ደግሞ ለቋሚ የአካል ጉዳት ይዳረጋሉ።

ሆኖም ግን ስትሮክ በቂ ክትትል ከተደረገለት የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መዳን የሚችል የጤና ችግር ነው፡፡

ለስትሮክ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል፦ ደም ግፊትና የስኳር ህመም፣ ጭንቅላት ላይ የሚደርስ አደጋ፣ የስብ ክምችትና ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ከልብ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የጭንቅላት ዕጢ፣ የደም መቅጠን እንዲሁም ሲጋራና አደንዛዥ ዕጾች ይጠቀሳሉ፡፡

የስኳር፣ የልብና የኮሌስትሮል ህመም ያለባቸው ሰዎች መድሃኒታቸውን በአግባቡ ካልወሰዱ ለስትሮክ የመጋለጣቸው እድል ሰፊ መሆኑም ይነገራል።

በተጨማሪም÷ የአልኮል መጠጥ አዘውትሮ መጠጣት፣ የሆርሞን መዛባትና የእድሜ መግፋት ለስትሮክ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የበሽታው ምልክቶች ራስ ምታት፣ የእጅ/የእግር መዛል፣ መድከም፣ የተወሰነ የሰውነት ክፍል አለመንቀሳቀስ ወይም ለመራመድ መቸገር፣ ለመናገር የአፍ መተሳሰር ወይም ቃላት ለማውጣት መቸገር እና የፊት መጣመም ይጠቀሳሉ፡፡

ስትሮክን ለመከላከል ከሚያስችሉ መንገዶች መካከል ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት መከተል እንደ ቅባት ጮማ የበዛባቸውን ምግቦች አለመመገብ፣ የአልኮል መጠጥ አለመውሰድ፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እና እንደ ደም ግፊት፣ የስኳር፣ የልብና የኮሌስትሮል ህመም ያለባቸው ሰዎች መድሃኒታቸውን በአግባቡ መውሰድ ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ በአቅራቢያ ወደሚገኙ የጤና ተቋማት በመሄድ የጤና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም ይመከራል፡፡