አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ባህር ሀይል በደቡባዊ ቀይ ባህር 12 የሃውቲ ድሮኖች መትቶ መጣሉን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንዳስታወቀው፥ የአሜሪካ ባህር ሀይል በደቡባዊ ቀይ ባህር ባደረገው ዘመቻ ሶስት ፀረ መርከብ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን፣ ሁለት ክሩዝ ሚሳኤሎችን እና 12 ድሮኖችን መትቶ መጣሉን አስታውቋል፡፡
ሚሳኤሎቹ በ10 ሰዓታት በሃውቲ ታጣቂዎች የተተኮሱ መሆናቸውን የገለፀው ማዕከላዊ ዕዙ፥ በፀረ ማጥቃት ዘመቻው በቀይ ባህር ላይ በሚገኙ መርከቦች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን አመላክቷል፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ይህን ይበል እንጂ የሃውቲ ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች በምትንቀሳቀስ አንድ መርከብ ላይ የሚሳዔል ጥቃት መፈፀማቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘም የሃውቲ ታጣቂዎች በተቆጣጠሩት የየመን ግዛት አካባቢ በሚገኘው የኢላት ወደብ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈፀማቸውን ፕሬስ ቲቪ ዘግቧል፡፡
ሃውቲዎች ለፍልስጤማውያን ድጋፍ ለማሳየት በሚል በቀይ ባህር ለእስራኤል ድጋፍ ያደርጋሉ ባሏቸው ሀገራት መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡
በዚህም በቀይ ባህር ላይ መስመር ላይ ከፍተኛ የደህንነት ውጥረት የተፈጠረ ሲሆን የቀይ ባህር ደህንነትን ለመጠበቅ አሜሪካ መራሽ ወታደራዊ ጥምረት መቋቋሙ የሚታወስ ነው፡፡